ኢየሱስ የመጣዉ በእርግጥ ለሁሉም ሰዉ ነዉ? Did Jesus Really come for Everyone?

ኢየሱስ የመጣዉ በእርግጥ ለሁሉም ሰዉ ነዉ?

Did Jesus Really come for Everyone?

(Scroll up for English version)

እኛ እንኳን እንደ ሰዉ ልጆች ሰዎች ወደ ህይወታችን እንዲገቡ ለመፍቀድ የየራሳችን መመዘኛዎች አሉን፡፡ አንድ ሰዉ ሰዉ ስለሆነ ብቻ ጓደኛችን፣ ሠራተኛችን፣ የሥራ ሽርካችን፣ የትዳር አጋራችን፣ ወዘተ. እንዲሆን አንፈቅድም፡፡ ከአንዱ ሰዉ ይልቅ ሌላዉን ሰዉ እንመረጣለን፡፡ ለኛ ትልቅ ቁም ነገር የሆነ ነገርን የሚያከብሩና የኛን እሴቶች የሚጋሩ ሰዎችን እንፈልጋለን፡፡

ለእግዚአብሔርስ ትልቁ ቁም ነገር ምንድነዉ? ሰዎችን በምን መስፈርት ይመርጣል? ሁሉንም ሰዉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚወድ እናዉቃለን፤ ድነትን በተመለከተ ግን “የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸዉና” ብሏል (ማቴዎስ 22¸14)፡፡ ጥቂቶችን ከብዙሃን ያስበለጠበት መስፈርት ምንድነዉ? ሰዎች ያሉበት የኃይማኖት ቡድን ነዉ? የሀጢአት ወይስ የጽድቅ ብዛት ይሆን? እድሜ? የጸሎት ርዝመት? የመጽሐፍ ቅዱስ እዉቀት? ወደ ቤተክርስቲያን ምልልስ ብዛት? ለቤተክርስቲያንና ለደሆች የሚሰጠዉ የገንዘብ መጠን ነዉ? ሁሉም ሰዉ መዳን ስለሚያስፈልገዉ ለምን እንዲሁ ሁሉንም አያድንም?

ዮሐንስ 5¸1-9

“ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ፣ አምስት ባለ መጠሊያ መመላለሻዎች የነበሯት፣ በአራማይክ ቋንቋ ቤተ ሰይዳ የተባለች አንዲት መጠመቂያ አለች፡፡ በእነዚህ መመላለሻዎች ዉስጥ ብዙ አካለ ስንኩላን፣ ዐይነ ስዉሮች፣ አንካሶችና ሽባዎች ይተኙ ነበር፡፡ … በዚያም ለሠላሳ ስምንት አመት ሕመምተኛ ሆኖ የኖረ አንድ ሰዉ ነበር፡፡ ኢየስሱም ይህን ሰዉ ተኝቶ ባገኘዉ ጊዜ፣ ለብዙ ጊዜ በዚህ ሁኔታ እንደነበር አዉቆ “ልትድን ትፈልጋለህ?” አለዉ፡፡

ሕመምተኛዉም መልሶ፣ “ጌታዬ ዉሃዉ በሚናወጥበት ጊዜ ወደ መጠመቂያዪቱ የሚያወርደኝ ሰዉ የለኝም፤ ለመግባት ስሞክር ሌላዉ ይቀድመኛል” አለዉ፡፡ ኢየሱም “ተነሥ! መተኛህን ተሸክመህ ሂድ” አለዉ፡፡ ሰዉየዉም ወዲያዉ ተፈወሰ፤ መተኛዉንም ተሸክሞ ሄደ፡፡”

በዚህ ታሪክ ዉስጥ ይህ ሰዉ ለ38 አመታት ሕመምተኛ እንደነበር እናያለን፡፡ ኢየሱስም ሰዉየዉ በዚህ ሁኔታ መቆየቱን አዉቋል፡፡ ታዲያ “ልትድን ትፈልጋለህ?” ብሎ መጠየቁ ለምን አስፈለገ? እርሱ አምላክ ነዉ ሊፈዉሰዉ ይችላል፡፡ ለምን እንዲሁ ያለምንም ጥያቄ እንዲህ ለረጅም ጊዜ ትልቅ ችግር ላይ የቆየዉን ሰዉ አልፈወሰም? በርግጥም ሰዉየዉን ፈዉስ ያስፈልጓል ነገር ግን ኢየሱስ ከአንደበቱ መስማትን ለምን አስቀደመ?

ከኢየሱስ ድህነትን ለማግኘት አንድ ሰዉ መታመሙ፣ ችግር ዉስጥ መሆኑ፣ ሀጢአተኛ መሆኑ ብቻ በቂ አይደለም፤ መዳንን በብርቱ መሻት አለበት፡፡ እንደዚያ ባይሆንማ ኖሮ የጠፋ ሰዉ ሁሉ ባለበት ድነትን ባገኘ ነበር፡፡

እጅግ የምንሻዉን ነገር ስናገኝ አመስጋኝ እንሆናለን፣ በአግባቡ እንጠቀምበታለን፣ እንወደዋለን፣ እንጠብቀዋለን፣ እግዚአብሔርን እናከብርበታለን፡፡ በብርቱ ለምንሻዉ ነገር ስንል የሚፈለገዉን ርቀት እንሄዳለን፣ የሚፈለገዉን ሁሉ እናደርጋለን – እንለወጥለታለን፡፡ ልባችን ከሁሉ በላይ ያላሻዉን ነገር ስናገኝ ቢበዛ ችላ እንለዋለን፤ ሲከፋ ደግሞ ለጥፋት እንዳርገዋለን፡፡ ኢየሱስ ሕመምተኛዉን ሰዉ የልቡ መሻት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ነበር የጠየቀዉ፡፡ “ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ በሩም ይከፈትላችኋል፡፡” (ማቴዎስ 7፡7) የሚለንም ለዚሁ ነዉ፡፡

ስንቶቻችን የዘላለም ህይወትን እንፈልጋለን? ስንቶቻችንስ የማንነት ድካማችንን አሸንፈን መልካም፣ አፍቃሪ፣ ትሁትና የተከበሩ ሰዎች መሆን እንፈልጋለን? ፀሎቶቻችን እንዲመለሱና ችግሮቻችን እንዲፈቱ የምንፈልግስ ስንቶች ነን? ግን ፍላጎታችን ከማንኛዉም በላይ የጠነከረ ነዉ? ችግራችሁ እንዲፈታ ነዉ የምትፈልጉት ወይስ ችግር ፈቺዉን ነዉ የምትፈልጉት? እግዚአብሔርን ነዉ ወይስ እግዚአብሔር የሚያደርግላችሁን ነዉ የምትፈልጉት?

በቀደመዉ ዘመን “…እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆኑ፣ እርሱም ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ብትፈልጉት ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን፣ ይተዋችኋል፡፡” (2 ዜና 15፡2) ይባል ነበር፡፡

ማቴዎስ 11፡28-30 “እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ አኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ፡፡ ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔም በልቤ የዋህና ትሁት ነኝና፤ ለነፍሳችሁ እረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነዉና፡፡”

ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ መሠረት የሚጠራዉ ሁሉንም ሰዉ ነዉ እንዴ? አይደለም፡፡ ሸክም የከበዳቸዉና የደከሙ! የምን ሸክም ነዉ? በምንስ ነዉ የደከሙት? እነዚህ ከእርሱ ጋር ትክክል መሆን፣ መልካም ምግባር እንዲኖራቸዉ፣ በዙሪያቸዉ ካሉ ሰዎች ጋር በሰመረ ግንኙነት መኖርን፣ መልካም ትዳርን መምራት፣ መልካም ምግባር ያላቸዉ ልጆችን የሚፈልጉ፣ በአጠቃላይ ዘላለማዊዉን ህይወት ለማግኘት ዘወትር መልካም ነገር ሁሉ ለማድረግ የሚጥሩ ነገር ግን አቅም የሌላቸዉ ናቸዉ፡፡ ይሞክራሉ ግን አይሳካላቸዉም፡፡ ከመስመር ላለመዉጣት ይጥራሉ ግን በሀጢአተኛ ተፈጥሮአቸዉ ይሸነፋሉ፤ ሀጢአታቸዉ ከአቅም በላይ ይሆንባቸዋል፡፡ መላ የጠፋቸዉ፣ የሰለቻቸዉ፣ የደከሙ፣ በማንነታቸዉ ተስፋ የቆረጡ ናቸዉ፡፡ መልካም ነገር ለማድረግ ሲሞክሩ ክፉ አድርገዉ ራሳቸዉን ያገኛሉ፡፡ የተሻለ እንደሚወጣቸዉ ተስፋ ሲያደርጉ ይልቁንም ይብሳሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች በአንድ ወቅት ጳዉሎስ እንደተሰማዉ የሚሰማቸዉ ናቸዉ፡-

“በእኔ፣ ማለትም ኀጢአተኛ በሆነዉ ተፈጥሮዬ ዉስጥ ምንም በጎ ነገር እንደማይኖር ዐዉቃለሁ፤ በጎ የሆነዉን የማድረግ ምኞት አለኝ፤ ነገር ግን ልፈጽመዉ አልችልም፡፡ የማደርገዉ ላደርገዉ የምፈልገዉን በጎ ነገር አይደለም፤ ዳሩ ግን ለማድረግ የማልፈልገዉን ክፉ ነገር ነዉ፡፡ ….ይኸዉም በጎ ነገር ለማድረግ ስፈልግ፣ ክፋት ከእኔ ጋር አለ፡፡ በውስጤ በእግዚአብሔር ሕግ ሀሤት አደርጋለሁ፤ ነገር ግን በብልቶቼ ውስጥ ለሚሠራዉ የኀጢአት ሕግ እኔን እስረኛ በማድረግ፣ ከአዕምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋ ሌላ ሕግ በብልቶቼ ውስጥ ሲሠራ አያለሁ፡፡ እኔ ምን አይነት ጎስቋላ ሰዉ ነኝ! ከዚህ ለሞት ከተሰጠዉ ሰዉነት ማን ሊያድነኝ ይችላል? በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ምስጋና ለእግዚአበብሔር ይሁን፡፡” (ሮሜ 7፡18-21)

ይህ ዓይነት ስሜት አድሮባችሁ ያዉቃል?

ኢየሱስ “የመጣሁት ለእናንተ ነዉ! ማድረግ ያለባችሁ ቀንበሬን መሸከም እና ከእኔ መማር ብቻ ነዉ” ይላል፡፡ ቀንበር ሁለት በሬዎችን ጎን ለጎን አንድ ላይ በመጥመድ በአንድነት እንዲያርሱ የሚረዳ የእርሻ መሣሪያ ነዉ፡፡ ስለዚህ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ከእኔ ጋር ተጠመዱ፣ ወደ ህይወታችሁ አስገቡኝና ቡድን እንሁን፣ ብቻችሁን ህይወትን መግፋትና ነፍስን ማሳረፍ ይከብዳችኋል፤ እኔ ልሸከምላችሁ፤ በሂደት ከእኔ ስትማሩ ህይወት ትቀላለች፣ ነፍስም ታርፋለች ማለቱ ነዉ፡፡

ስለዚህ ደክሟችኋል? ሸክም ከብዷችኋል? የምሥራች! ኢየሱስ የመጣዉ ለእናንተ አይነቱ ነዉ፡፡ ህይወት እናንተ እንዳሰባችሁት የሆነችላችሁና ምንም እርዳታና ለዉጥ የማያስፈልጋችሁ ከሆነ ግን ኢየሱስ ለእናንተ አይደለም፡፡

ማቴዎስ 21፡28-32

“ኢየሱስ እንዲህ አላቸዉ፤ “ምን ይመስላችኋል? ሁለት ወንዶች ልጆች ያሉት አንድ ሰዉ ነበረ፤ ወደ መጀመሪያ ልጁ ሄዶ፣ ‘ልጄ ሆይ፤ ዛሬ ወደ ወይኑ ቦታ ሄደህ ሥራ’ አለዉ፡፡ ልጁም፣ ‘አልሄድም’ አለዉ፤ ኋላ ግን ተጸጽቶ ሄደ፡፡ ወደ ሁለተኛዉ ልጁ ሄዶ እንደዚያዉ አለዉ፤ ልጁም ‘እሺ ጌታዬ እሄዳለሁ’ አለዉ፤ ነገር ግን ሳይሄድ ቀረ፡፡ “ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመዉ የትኛዉ ነዉ?” እነርሱም “የመጀመሪያዉ ልጅ” አሉት፡፡ ኢየሱስም፤ “እዉነት እላችኋለሁ፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድማችኋል፤ መጥመቁ ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ ወደ እናንተ መጣ፤ እናንተ አላመናችሁትም፤ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች ግን አመኑ፡፡ የሆነዉን ካያችሁ በኋላ እንኳ ንሰሓ ገብታችሁ አላመናችሁም፡፡”

ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የሰጠዉ ለካህናት አለቆችና ለሕዝብ ሽማግሌዎች ነበር፡፡ እነዚህ ራሳቸዉን ትክክለኛ ኃይማኖት የያዙና ወደ እግዚአብሔር የቀረቡ ጻድቃን አድርገዉ ይቆጥሩ ነበር፡፡ ምናልባትም ኢየሱስ ቀረጥ ሰብሳቢዎች (ሙሰኞች) እና አመንዝራዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ቀድሞአችሁ በመግባት ላይ ናቸዉ በማለቱ ሳይቀየሙ አይቀርም፡፡ እኛስ? መልካም ሰዎች ለመሆን፣ የእግዚአብሔርን ህግ በማክበርና በማስከበር የምናደርገዉ ጥረት ሁሉ ከንቱ ነዉ? የግድ እንደ እነዚያ ሰዎች ኃጢአተኛ መሆን አለብን እንዴ? የሚሉ ጥያቄዎችን ሳያነሱ አለቀረም፡፡

የኢየሱስ ነጥብ ግን ወደ መንግስቱ የሚገቡት ኀጢአተኛ መሆናቸዉን አምነዉ የራሳቸዉ መልካምነት እንደማያድናቸዉ የተቀበሉ፣ የእርሱን አዳኝነት አጥብቀዉ የሚሹ ናቸዉ፡፡ እንደ መጀመሪያዉ ልጅ ከአባቱ ጋር ያለዉን ግንኙነት ለማክበር የልብ ለዉጥ ማድረግ እንጂ እንደ ሁለተኛዉ ልጅ ትክክለኛ መልስ መስጠት አያድንም ማለቱ ነዉ፡፡ ንሰሃ የሚገባ ኀጢአተኛ ንሰሃ ከማያስፈልገዉ “ጻድቅ” ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት አለዉ፡፡ ማርቆስ 2፡17 ላይ ኢየሱስ በግልጽ “ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ወደ ንሰሓ ልጠራ አልመጣሁም” ብሏል፡፡

ምንም እንኳን ሁሉም ሰዉ ሀጢአተኛና የጠፋ ቢሆንም ኢየሱስ ግን የሚያድነዉ ሁሉንም አይደለም፡፡ እንደ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች የሀጢአት ሸክም የከበዳቸዉና የደከሙ፣ በሰዎች የተናቁና የተገለሉ፣ ስለራሳቸዉ ማንነት ደስ የማይሰኙ፣ ብቻቸዉን መለወጥ እንደማይችሉ የተቀበሉና አዳኝ እንደሚያስፈልጋቸዉ ያመኑ መሆን አለባቸዉ፡፡ እርስዎስ “ጻድቅ” ነዎት ወይስ አዳኝ ያስፈልግዎታል?

የሚድኑት ሀጠአተኞች ናቸዉ ስንል ሄደን ሀጢአት ዉስጥ እንዘፈቅ ለማለት ሳይሆን ራሳችንን እንድናዋርድ፣ በመልካም ተግባራችን ላይ እንዳንደገፍ ይልቁንም ከእግዚአብሔር ምህረትን ለማግኘት ንሰሓ መሻት እንድንችል ነዉ፡፡

ኢየሱስ የመጣዉ ለመልካም ሰዎች ሳይሆን ማንኛዉንም ዋጋ ከፍለዉ ከእርሱ ጋር ለመጠመድ ዝግጁ ለሆኑ ፈላጊ ሀጢአተኞች ነዉ፡፡ እርስዎ ፈላጊ ሀጢአተኛ ነዎት ወይስ ወደ ገነት ለማቅናት የሚጠባበቁ መልካም ሰዉ ነዎት?

ምናልባት እኔ ክርሰቲያን ነኝ፤ ቀድሞዉኑ ወደ ኢየሱስ ሄጄ ቀንበሩን አንስቼአለሁ ብለዉ ያስቡ ይሆናል፡፡ መልካም! ግን ክርሰቲያን መሆንዎ የበለጠ ፈላጊ፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በእርስዎ ዉስጥ የተወለደዉ ክርስቶስ እንዲያድግ ትጋትዎን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው? ምን ያህል ከክርስቶስ እየተማሩ ነው?  ምን ያህል በህይወትዎ የዓላማ ለውጥ አለ? እርሱ ቃል እንደገባው ውስጥዎ ምን ያህል ሰላም አለ?

የኢየሱስን የማዳን እቅድ ለመረዳት ልባዊ መሻቱ ካለዎትና እርዳታ ቢያስፈልዎ መንገዱን በቃሉ መሠረት ብንጠቁምዎ ደስ ይለናል፡፡ እባክዎ መልዕክት ይላኩልን፡፡

ጌታ ወደ ራሱ ከሚጠራቸዉ መካከል አንዱ ያድርግዎት! ስለሰሙን እናመሰግናለን!!

Did Jesus Really come for Everyone?

Even as human beings, we have a set of criteria to allow people into our lives. We do not let them become our friends, our employees, business partners, spouses, etc. just because they are humans. We prefer some people over others. We look for people who respect what matters to us and who share our values.

How about God? What matters to him? We know he loves everyone unconditionally, and is inviting everyone to his kingdom but He says he chooses only a few to be SAVED (Matthew 22:14). What makes him choose some over others? Is it people’s religious affiliation? Is it a number of sin? Age? Number of good things people have? Length of prayer? Knowledge of the Bible? Is it how often one goes to church? Or How much money they give to church and to the poor? Why doesn’t he just save everybody because they all need it anyway?

John 5:1-9 In this passage, we see that the man had been an invalid for 38 years and Jesus could tell. Jesus is God and could heal him but why was it important to ask “Do you want to get well?” The man is helpless; of course, he needs to get well. But why did Jesus want to hear it from the man’s mouth first? To Jesus, being in need is not enough to grant salvation; you gotta seek it.

When we find something we really seek, we are grateful, we use it properly, we cherish it, we protect it and we honor God with it. When you seek something, you are willing to go the distance for it, do anything for it – you are willing to change for it. Whatever we find without seeking will be taken for granted at best and will be abused at worst. That is why Jesus is asking the invalid. That is why he says to us all, “seek and you will find, knock and the door will be opened, and ask and you will be answered” (Matthew 7:7-11).

How many of us want to go to heaven? How many of us want to overcome our weakness and really become good, loving, humble, respectable people? How many of us want our prayers to be answered and problems to be solved? But do you want or you seek? Do you just want your problem solved or you want the problem solver? Do you want God or just the things that God can do for you? In the olden days, it was said: “…the LORD is with you when you are with him. If you seek him, he will be found by you, but if you forsake him, he will forsake you” (2 Chronicles 15:2).

Matthew 11:28-30 who is Jesus reaching out to here? Everybody? No. The weary and Burdened! Weary and burdened with what? People who really want to be right with him, have good character, lead good relationships with people around them, good marriage, good kids, always do the right thing and eventually make it to eternity but can’t do it. They try but keep failing. They want to hold it together but are overpowered by sinful nature and overwhelmed by sins in their lives. They are desperate. Tired. Burdened. When they try to do the right thing, they end up doing the wrong one. When they hope for the best in them, their worst happens instead. They feel as Paul felt (Romans 7:18-24). Ever felt like that?

Jesus says, “I am here for you! All you have to do is: take my yoke upon you and Learn from me.” Yoke is an agricultural tool to tie two oxen together and plow the land. So, in other words, Jesus is saying be yoked with me, team me up in your life, invite me in. Without me, life is too hard for you and your soul has no rest; let me help you and then as I walk with you, you look at me and learn from me. Then life will be easy and your soul will find rest.

So, are you weary and burdened? Good News! Jesus is here for you! If you think you have it all together and life is going well, it needs no help or change, he is not for you.

Matthew 21:28-32

Jesus was talking to the high priests and the elders of the people and giving them this parable. These people considered themselves to have the correct religion and righteous people who were close to God. When Jesus said that tax collectors (greedy) and prostitutes were entering the kingdom of God ahead of them, they must have felt offended. They must have asked themselves: How about us? How about all the hard work we have been putting in to honor the law of God and get it honored? Is it all in vain?

Jesus’ point is that those who enter his Kingdom are people who believe that they are sinners, that their own goodness won’t save them and hence, seek the Savior. Making the change of heart like the first son in honor of his relationship with his father is what saves, not knowing/having the right answer like the second son. A repentant sinner is justified before God better than a “saint” who does not need to repent. In Mark 2:17, Jesus said, “I have not come to call the righteous, but sinners”.

Even if all are sinners and need to be saved, Jesus will not save everyone. Just like tax collectors and prostitutes, they need to be weary and burdened by their sins, despised by others, social outcasts who feel terrible about themselves, admit that they cannot change by themselves and hence, believe and seek a savior. How about you? Are you a “saint” or a sinner who needs a savior?

This is not an encouragement to get wild in life and indulge in sin but a call to be humble and not to rely on how good we are and seek repentance and mercy from God.

Jesus did not come to save good people but people who believe that they are sinners and need help, people who seek to be yoked with Jesus at any cost. Jesus came to save sinners that are Seekers! Are you a seeker or just a good settler?

Perhaps, you may say that you are a Christian; you have already gone to Jesus and taken up his yoke. Great! But has the fact that you are a Christian made you a better seeker? Has it increased your devotion from time to time to grow the person of Jesus  Christ who was born in you through the Holy Spirit? How much are you learning form him? Have you made a change of purpose in your life? As he promised, is your soul at peace?

If you truly seek to understand the saving plan of Jesus and need help, we will be more than happy to direct you to his path according to the scriptures.  Please send us a message.

May the Lord make you one of those He will draw to himself! Thank you for listening to us!

Comments are closed.